29/03/2026
ኒቆዲሞስ፡ የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት
በመ/ር ጌታቸው በቀለ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሠረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት፣ የሚነበበው ወንጌል “ኒቆዲሞስ” ን የሚያወሳ ነው። /ዮሐ ፫፥፩-፳፩/፡፡
ኒቆዲሞስ ማን ነው?
ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ኒቆዲሞስ ማለት ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል፡: ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት እንደተገለጸው ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው እንደነበረና እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ እንደተማረ ተጠቅሷል /ዮሐ ፩-፪/፡፡
ኒቆዲሞስ የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን ሥልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በሕዝቡ ላይ የሚመጻደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ዕውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትሕትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ፣ ይከስሱ ነበር፡፡ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሐሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሠሩ አስጠንቅቋቸዋል /ማቴ.፭፥፳፤ማቴ. ፲፮፥፮/፡፡
ኒቆዲሞስ ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ከፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ ከሁሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ እንደ አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙሪያው የነበሩ “ከእኛ በላይ ማን ዐዋቂ አለ?” የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱትን ንቆ እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትሕትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትሕትናውን ተቀብሎ “ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡
ኒቆዲሞስ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር ቀብሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረዉ ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀበርበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ።” እንዳለ /ዮሐ ፲፱፥፴፱/። በዚህም ኒቆዲሞስ ከምክረ አይሁድ ያልተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል።
ኒቆዲሞስ የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ?
ኒቆዲሞስ በመጀመሪያ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በቀን ሳይሆን በሌሊት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታችን ከሄደባቸው ምክንያቶች አንዱ በቀን መሄድን ስለፈራ ነው። ለዚህም የቤተ ክርሰቲያን አባቶች በዋናነት ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመሪያው የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ በቀን በሕዝብ ፊት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ስላፈረ ነው የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ “ከእኛ ወገን በክርስቶስ ያመነ ቢኖር ከምኩራብ ይሰደድ” የሚል ዐዋጅ ዐውጀው ነበርና ያንን ፈርቶ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፍራቻዎች ኒቆዲሞስን ወደ ክርስቶስ ከመምጣት አላገዱትም፡፡
ኒቆዲሞስ በርቀት በአደባባይ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግ ያየውን ኢየሱስ ክርስቶስን ቀርቦ መጠየቅ መማር ፈልጓል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት የተረዳው ነገር ቢኖርም ቀርቦ ደግሞ ከእርሱ ከራሱ ስለማንነቱ መስማት ፈልጓል፡፡ ወደ ክርስቶስም ቀርቦ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው /ዮሐ.፫፥፪/፡፡
ኒቆዲሞስ ቀን ቀን በአይሁድ ወንበር በሸንጎ እየዋለ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ጌታችን ዘንድ እየመጣ ቃለ ወንጌልን ይማር ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ መምህር ስለነበር ስማር ብዙ ሰዎች ሲያዩኝ በውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ፤ የአይሁድ መምህር ስለነበር እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ከቀን ልብ ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ፡፡ ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃን የለም ጨለማ የኃጢአት ምሳሌ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሐ እንደሚፈልግ የሚያስረዳን ነው፡፡ሌሊት የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው፡፡ ኒቆዲሞስም “እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም ፡፡ ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል” ሲል በሌሊት ይመጣ ነበር፡፡ ብሉያት ከሐዲሳት ጋር ተዋሕደው ሲተረጎሙ ሰሙና ወርቁ ተጣምሮ የሕይወት ትምህርት ያስገኛል፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰዓት ለመማር ችሏል፡፡
ዳግመኛ የመወለድን ምስጢር
ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው፣ ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትሕትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትሕትናውን ተቀብሎ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ /ምሳ 9፥11/ ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ኅብረት ወጥቶ በትሕትና ወንጌልን ለመማር፣ በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትሕትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡
ስምዐ ጽድቅ
ኒቆዲሞስ ወደ መድኃኔዓለም ለመማር የሄደው በሌሊት ነበር፡፡ ሌሊት በባሕሪው ሕሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው፡፡ ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ” በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል /ዮሐ.፲፰፥፴፯/፡፡ በተጨማሪም “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል /ማቴ.፲፥፴፪-፴፫/፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን” በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል /ዮሐ.፫፥፲፩/፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል /ዮሐ.፯፥፶-፶፪/፡፡ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት ለታላቅ ክብር በቃ፡፡
ጌታን ለመገነዝ የበቃ
በጌታችን ትምህርት ተስበው ተአምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ ከተገኙት አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ጻድቅ ነው፡፡ ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው /ዮሐ.፲፱፥፴፰/፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋሕዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍጻሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምስጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” /ቅዳሴ ማርያም፤ ቁ.115/ ብሏል፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም “መምህር ሆይ” ብሎ የእርሱን አላዋቂነት የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዐትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ፣ ቀራንዮ የነበረ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ሥጋ የገነዘ፣ ወደ ሐዲስ መቃብ ር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ ፣ ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ሥር ቁጭ አለ፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ በዕውቀታችን፣ በሥልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሣጽ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ብዙ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምስጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ በቅዳሴው በኪዳኑ በሰዓታቱ በማኅሌቱ መገኘትና መሳተፍ ረቂቅ የሆነው ሰማያዊ ምሥጢር አንዲገለጥልን ምክንያት ነውና በምሥጢራት በመሳተፍ ራስን ዝቅ በማድረግ ለታላቅ ክብር እንድንበቃ መትጋት ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” /ማር.፲፮፥፮/ በማለት በሰጠን ቃል ኪዳን መሠረት በአምላክነቱ አምነን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ይፍቀድልን፤ ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን እንደ ገለጸ ለእኛም ይግለጽልን፤ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ሃይማኖተ አበው
✍️ ቅዳሴ ማርያም
✍️ የቤተክርስቲያን መዝገበ ቃላት
✍️ ጾም ምጽዋት
✍️ በዓላት ለምን፣እንዴት?