
19/04/2025
የጴጥሮስ ዶሮ (ወንጌል ሰባኪ)
ከሐዋርያቱ መካከል በዕድሜው አንጋፋ ክርስቶስ ሲጠራው 55 ዓመት የነበረው፣በወንድሙ እንድርያስ አማካኝነት ወደ ጌታ የቀረበ፣
ለክርስቶስ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ፣
አረጋዊ ቅን የሆነ ፍፁም ትሁት ሐዋርያ፣
አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ የመሰከረ፣
ከሐዋርያቱ የመጀመሪያው ለአህዛብ ወንጌልን የሰበከ፣
ለክርስቶስ ካለው ፍፁም ፍቅር የተነሳ ጌታ እሞታለሁ ሲላቸው አይሁንብህ፣በማለት የተከራከረ ጌታችንም የገሰፀው፣ከወንድሞቹ ሐዋርያት ጋር ሆኖ ዓለምን በወንጌል ያበራ፣
የሐዋርያት አለቃቸው፣የቤተክርስቲያን ዓለት ነህ በአንተ ላይ ቤተክርስቲያን ትሰራለች የተባለው።
ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን መድሃኒታችን በተያዘ ሌሊት በዚያ የመከራ ሰዓት፣
ከመከራው ፅናት የተነሳ ሌሊቱ ረጅም በሆነበት ወቅት፣ሌሎቹ ሐዋርያት በጌታ መያዝ ወዲያና ወዲህ በተበታተኑበት ሰዓት፣ይሁዳ ከአይሁድ የወሰደውን ሠላሳ ዲናር በሚቆጥርበት ሌሊት፣
ማርቆስ አይሁድ ሲይዙት የለበሰውን ነጠላ እጃቸው ላይ፡ጥሎ ዕርቃኑን ሲፈረጥጥ፣
እናቱ ድንግል ማርያም የሃዘን ሰይፍ ነፍሷን ሲያሰቃያት፣
እነማርያም መግደላዊት በፍርሃትና ረዓድ ሆነው ሲጨነቁ፣
ዮሐንስ ፊቱ በሃዘን ሲጠቁር ሲያለቅስ ።
በዚያ አስጨናቂ ሌሊት የአይሁድ ወታደሮች ወይን እየጡጡ ሲሳሳቁ፣
በክርስቶስ ጀርባ አለንጋ ሲወርድ፣
ንጉስ ሆይ ሺህ ዓመት ንገስ በማለት የእሾህ አክሊል እያደረጉለት ሲዘባበቱ፣ለህይወት ውሃ ውሃ ሲከለክሉት፣
ጴጥሮስ ከአይሁዳውያኑ መሃል ሆኖ እሳት እየሞቀ አይተንሃል ከእርሱ ጋር ነበርክ፤የእርሱ ደቀመዝሙር ነህ ፣ከእርሱ ወገን ነህ፣
ንግግርህ ይመሰክራል ሲባል የምትሉትን አላውቅም ።
በማለት ዶሮ አንዴ ሳይጮኽ ሦስቴ ካደው።
ከሦስት ክህደት በዃላ ዶሮ አንዴ ጮኸ፡፡ጴጥሮስም ያኔ ነቃ ፤የጌታው ቃል ትዝ አለው።
ተፀፀተ አለቀሰ አብዝቶ አነባ ፍቅር የሆነው አምላክ ኢየሱስም ፀፀቱን ተቀብሎ እንባውን መዝኖ የበለጠ ሾመው የበለጠ አከበረው የበለጠ ወደደው።
ግን ያ ዶሮ በአንድ ጩኸት ጴጥሮስን ያነቃ ያ ዶሮ ምን አይነት ዶሮ ይሆን? ምንስ አይነት ጩኸት ምንስ ዓይነት ስብከት ነው ያሰማው?
የጴጥሮስስ ልብ እንዴት ያለው ቅን ልብ ነው?የተዘጋጀ ለንሰሃ ቅርብ የሆነ አምላኩን የሚወድ እንደ ይሁዳ ያልጠመመ፣
እንደ ፈርዖንም ያልደነደነ
መልካም እርሻ የሆነ እንዴት የተባረከ ልብ ነው?ዛሬ በየቤተክርስቲያኑ ብዙዎች እንደዶሮው እንጮኻለን፣
ሰሚ የለም፣ምክንያቱም ጩኸታችን የማስመሰል ራስን የመስበክ ዝና ፍለጋ ነውና።
ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ነው።
ሰሚየሌለው እንደ ጴጥሮስ ለንሰሃ ሳይሆን የተዘጋና የተቆለፈ ልብ ይዘን ስለሐጢዓታችን ንሰሃ ሳንገባ ስንት ሌሊት ስንት ቀናት አለፉ ።
ዶሮዎቹ ወይም ሰባክያኑ ስለአጯጯኻቸው (ስለስብከታቸው) ቃላት መረጣ እና ፕሮቶኮል ሲጨነቁ፣
ሰሚዎቹም (ምዕመናኑ)በዶሮዎቹ /በሰባክያኑ/ጩኸት ሲደነቁ ብዙ ዘመናት አለፉ፡፡
ጌታሆይ እንደ ጴጥሮስ ቅን ልቦና፣እንደ
ዶሮዉም ለንሰሃ የሚያበቃ አገልጋይ ስጠን።