
12/03/2025
በምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ቀሪ ስራዎች ዙሪያ ከአገራቱ አምባሳደሮች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡
ግንቦት 26/2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
በኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተባባሪ አካላት ከሰኔ 7 እስከ 12/2014 ዓ.ም ‹‹ጥበባትና ባህል ለቀጠናዊ ትስስር!›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ላይ ከሚሳተፉ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በፌስቲቫሉ ዝግጅት ዙሪያ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፡- የጥበባትና ባህል ፌስቲቫሉ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለመፍጠር እና የባህል ዲፕሎማሲን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰው ፌስቲቫሉ በዐውደ ጥናት፣ በዐውደ ርዕይ እና በልዩ ልዩ ባህላዊ ሁነቶች እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡››
በውይይቱ የተሳተፉት አምባሳደሮችም ፌስቲቫሉ የሀገራትን ጥበብና ባህል ለማስተዋወቅ እና ቀጠናዊ ገፅታን ለመገንባት ስለሚጠቅም ወቅታዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ አስፈላጊውን ተሳትፎ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር ሚንስትሩ ውይይቱን ሲያጠቃልሉ ከዚህ ቀደም ከሀገራቱ ተወካዮች ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደነበር ገልፀው ዛሬ እንድንገናኝ ያስፈለገበት መሰረታዊ ጉዳይ ሀገራቱ ሁኑቱን አስመልክቶ በተለይም ተሳታፊ ልዑካ ቡድኖች እንዲገኙ ከማድረግ አንፃር ስራው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማወቅ በቀጣይ ለምናካሂደው ሁነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡