
06/06/2025
የጥላቻ ንግግር የወንጀል ተጠያቂነት
~~~~~~
🎤ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡
🎤የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ እስከ ሁለት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 100ሺ ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
🎤በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል።
👉የሐሰት መረጃን ማሰራጨት ስለመከልከሉ
ማንኛውም ሰው የሐሰት መረጃን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ተግባር ነው፡፡
ማንኛውም ሰው ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እስከ አንድ አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር ፶ሺ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
🎤የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር ፻ሺ ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል፡፡
🎤ሐሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ከሁለት እስከ አምስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል።
🎤በጥላቻ ንግግር ወይም በሐሰተኛ መረጃ ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን ይችላል።
👉የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም፦
🖌"ንግግር” ማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልእክትን የማሰራጨት ተግባር ነዉ፣
🖌"የጥላቻ ንግግር" ማለት በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ነው፣
🖌"ሐሰተኛ መረጃ" መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው፣
🖌"ብሮድካስት ማድረግ" ማለት በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ሥርጭት ማድረግ ነው፣
🖌"መድሎ" ማለት ብሔርን ብሔር ብሔረሰብን ህዝብን ሃይማኖትን ዘርን ፆታን አካል ጉዳተኝነትን ወይም ሌሎች በህግ የተጠበቁ ልዩነቶችን መሰረት በማድረግ የሚፈጸም የማግለል ተግባር ነው፤
🖌"ጥቃት" ማለት በግለሰብ ወይም በቡድን አባላት ንብረት፣ አካል ወይም ሕይወት ላይ የሚፈጸም ጉዳት ነው፣
🖌"ማሰራጨት" ማለት ንግግርን በማናቸውም መንገዶች ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ ማድረግ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ ላይክ ማድረግና ታግ ማድረግን አያካትትም፣
🖌"ማህበራዊ ሚዲያ" ማለት ሰዎች መልዕክት ለመለዋወጥ ትስስር ለማዳበር ሀሳብ ለመጋራት የሚጠቀሙበት በኢንተርኔት አማካኝነት በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ለሆኑ ሰዎች መረጃ የሚደርስበት፣ ወይም ማህበራዊ መስተጋብር የሚስተናገድበት መንገድ ነዉ፣
🖌"የህትመት ሚዲያ" ማለት ለህዝብ ስርጭት የተዘጋጀ ማንኛውም የህትመት ወጤት ነው፣
🖌"ማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት" ማለት የማህበራዊ ሚዲያ አውታርን ወይም መድረክን ለተጠቃሚዎች የሚያደርስ ድርጅት ነው።