05/07/2026
ለስልጤ የማንነት ታጋይ ለሀሰን ኢብራሂም የገራድነት ማዕረግ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በድምቀት ተካሄደ!
በስልጤ ዞን በሚቶ ወረዳ የስልጤ ሕዝብ የማንነትና የልማት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ላበረከቱት ታዋቂው የማንነት ታጋይ ሀሰን ኢብራሂም የላቀ የባሕላዊ አመራርና የክብር መገለጫ የሆነው የገራድነት ማዕረግ የመስጠት ፕሮግራም ተካሂዷል።
የሚቶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከድር መሀመድ "ታጋይ ሀሰን ኢብራሂም የስልጤ ህዝብ በታሪኩ ውስጥ የራሱን አሻራ አሳርፎ፣ ማንነቱ ተከብሮና መብቱ ተረጋግጦ ዛሬ ለደረሰበት የልማትና የዕድገት ምዕራፍ እንዲበቃ ካደረጉ እውነተኛ የህዝብ ልጆች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ በመሆናቸው ማዕረግ ለሰሩት ታላቅ ሥራና ለከፈሉት መስዋዕትነት የሚመጥን ተገቢ እውቅና ነው፤"ብለዋል።
ታጋይ ሀሰን ኢብራሂም የስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ሕዝቡ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ ተከብሮ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር በነበረው ረጅም የትግል ጉዞ ውስጥ የማይተካና ታሪካዊ ሚና የነበራቸው መሆኑ ተገልጿል።
የታጋይ ሀሰን ኢብራሂም የገራድነት ማዕረግ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት፣ ወጣቱ ትውልድ ለማኅበረሰቡና ለሀገር ዕድገት በታማኝነት፣ በቅንነትና በቁርጠኝነት ማገልገል እንዳለበት ትልቅ የሕይወትና የሞራል ትምህርት ያስተላለፈ ክስተት መሆኑ ተገልጿል።
ታሪክ የማይረሳው ሥራ የሠሩ ባሕላዊና ማኅበራዊ መሪዎችን ማክበር የነገውን ትውልድ ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ መሆኑም ተጠቅሷል።